የዲስክ መንሸራተት ማለት በሁለት የጀርባ አጥንቶች መካከል የሚገኘዉና የአጥንቶቹን ንክኪ የሚቀንሰዉ ዲስክ ወደፊት ወይም ወደኃላ አሊያም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ በኩል ቦታዉን ለቆ በሚንሸራተትበት ወቅት የሚመጣ ነዉ፡፡


የህመሙ ምልክቶች
ስለመከሰቱ ምንም እዉቅና ሳይኖርዎ ወይም ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ሳይኖር የዲስክ መንሸራተት ሊኖር/ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ሳያሳዩ በምርመራ ወቅት በራጅ ላይ የዲስክ መንሸራተት መኖሩ ሊታወቅ ይችላል፡፡ የዲስክ መንሸራተት በሚኖርበት ወቅት የሚኖሩ የህመም ምልክቶች:-
• የእጅ/የእግር ላይ ህመም፡- የዲስክ መንሸራተቱ ያጋጠመዉ በታችኛዉ የጀርባ አጥንቶች አካባቢ ከሆነ ከፍተኛ ህመም በመቀመጫዎ፣ በጭንዎና በባትዎ አካበቢ እንዲሁም መርገጫዎ/የእግር መዳፉ ላይ ሊሰማዎ ይችላል፡፡ የዲስክ መንሸራተት ያጋጠመዎ አንገትዎ ላይ ከሆነ ህመሙ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማዎ በትከሻና በእጅዎ ላይ ነዉ፡፡ ሕመሙ በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበት ወቅት ወይም ወደ ተወሰነ አቅጣጫ የጀርባ አጥንቶችዎን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት ሊባባስ ይችላል፡፡
•የመደንዘዝ ወይም የመጠቅጠቅ ስሜት
•የእጅ/ እግር መስነፍ፡- በዲስክ መንሸራተት ምክንያት የተጎዳ ነርቭ ካለ ያ የተጎዳዉ ነርቭ እንዲሰራ የሚያደርገዉ ጡንቻ ሊደክም ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ መራመድ መቸገር፣እቃ ማንሳት ያለመቻል ወይም መያዝ ያለመቻል ሊከሰት ይችላል፡፡
የህክምና ባለሙያዎን ምምከር የሚገባዎ መቼ ነዉ


የጀርባዎ ህመምዎ ወደ እጅዎና እግርዎ የሚሰራጭ ከሆነ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
• የሰዉነት ክብደት፡- ክብደትዎ ከመጠን በላይ የጨመረ ከሆነ በጀርባ አጥንተትዎና ዲስኩ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡
• የስራዎ ሁኔታ፡- የስራቸዉ ፀባይ ጉልበት የሚጠይቅ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከባድ ነገር የሚያነሱ፣ የሚጎትቱ፣ የሚገፉ፣ ወደ ጎን መታጠፍና መጠማዘዝ የሚያበዙ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
• በዘር የሚመጣ፡- አንዳንድ ሰዎች ለመሰል ችግር ተጋላጭነታቸዉ መጨመር በዘር ሊወረስ ይችላል፡፡
የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥና የቤት ዉስጥ ህክምና
• የህመም ማስታገሻ፡- ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ እንደ አይቡፕሮፌን/አድቪል/ መዉሰድ
• ሙቀት/ቀዝቃዛ ነገር መጠቀም፡- በመጀመሪያ ቀዝቃዛ ነገር ቦታዉ ላይ መያዝ ህመሙንና መቆጥቆጡን እንዲቀንስ ይረዳል፡፡ ከተወሰኑ ቀናት በኃላ ሙቅ ነገር መያዝ ምቾትና የህመም ፈዉስ እንዲሰማዎ ስለሚያደርግ በቦታዉ ላይ መያዝ
• ከመጠን ያለፈ እረፍት ያለማድረግ/ማስወገድ፡- ከመጠን ያለፈ እረፍት የመገጣጠሚያዎች መጠንከር/መተሳሰር እና ጡንቻዎች መስነፍ እንዲመጣ ስለሚያደርግ የፈዉሱን ጊዜ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይልቁንም በሚመችዎ አቅጣጫ ለ30 ደቂቃዎች እረፍት ማድረግና ከዚያን ለአጭር ጊዜ ወክ ማድረግ አሊያም የተወሰኑ ስራዎችን ማከናወን፡፡ ከህመምዎ እያገገሙ ባሉበት ወቅት ህመሙን ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች/እንቅስቃሴዎች መቆጠብ፡፡
የዲስክ መንሸራተትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡- የጀርባ ጡንቻዎችን ለማጠንከር ስለሚረዳ የጀርባ አጥንቶችን ለመደገፍና ለማረጋጋት ይረዳል፡፡
• ትክክለኛ የሰዉነት አቋም/ Maintain good posture / እንዲኖርዎ ማድረግ፡- ጥሩ የሰዉነት አቋም ካለዎ በጀርባ አጥንትዎና ዲስኩ ላይ የሚመጣዉን ጫና ለመቀነስ ይረዳዎታል፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡ ከሆነ ቀጥ ብለዉ ለመቀመጥ መሞከር፡፡ ከባድ እቃ በሚያነሱበት ወቅት ስራዉን/ክብደትዎን ከጀርባዎ ይልቅ በእግሮችዎ ላይ ማድረግ፡፡
•ክብደትዎን በትክከል መጠበቅ፡- ከመጠን ያለፈ ክብደት በጀርባ አጥንትዎና ዲስክዎ ላይ ጫና ስለሚፈጥር ክብደትዎን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡